በባሕር ዳር ከተማ እየተሰራ ያለው ደንገል ማስፋፋት ፕሮጀክት ተጎበኘ
የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ከሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ተፋሰሶችን ከቆሻሻ ለመታደግ እና የጣና ሐይቅን ስነምዳር ለመጠበቅ ዓላማ አድርጎ እየተሰራ ያለውን የደንገል ማስፋፋት ፕሮጀክት የዩኒቨርስቲው አመራር አካላት ጎብኝተውታል፡፡
የደንገል ፕሮጀክት አስተባባሪ እና የቋንቋ መምህር የሆኑት ዶ/ር ንብረት አስራዶ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የጣና ሐይቅ ወደ ነበረበት መመለስ እና በከተማው ውስጥ የሚገኙ ተፋሰሶችን ከቆሻሻ ለመታደግ አላማ አድርጎ እየተሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የደንገልን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማሳየት የአካባቢውን ህብረተሰብ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በመነጋገር አካባቢውን ለማልማት የሚያግዙ የተደራጁ ወጣቶችን በሀላፊነት እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ያገኘናቸው አቶ ዘለቀ መኮነን እንደተናገሩት በጣና አካባቢ ከ1957 ዓ/ም ጀምሮ እንደሚኖሩ ተናግረው በፊት ከሚሰሙት በመነሳት ጣና እየተመናመነ ስለሆነ ከዚህ ጉዳት ለመታደግ እነደ አካባቢ ጥበቃ ማዘጋጃና ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡