የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም የመጀሪያ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ስልጠና ሰጠ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ለተቋሙ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ሰኔ 15 እና 16 2009 ዓ.ም የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ስልጠና በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ሰጠ፡፡
የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ዋና ዓላማው አድርጐ እየሰራ ያለው መማር ማስተማር፣ ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት እንደሆነ እና ይህ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ስልጠናም የማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ አካል መሆኑን እና ስልጠናው አዳጋ ሲደርስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የሚከሰት ጉዳትን መቀነስ እንዲቻል ታስቦ የተሰጠ እንደሆነ የተቋም መምህርና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ታረቀኝ አያሌው ገልፀዋል፡፡
አስተባባሪው አክለውም በዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከውጭ ማህበረሰብ ዘንድ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ እንዴት እንደሚሰጥ ግንዛቤ ባለመኖሩ የተለያዩ ችግሮች እንደሚፈጠሩ እና ክብር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ለህልፈተ ሞት እንደሚዳረግ ገልፀው ስልጠናው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የመጡ ተማሪዎች ጨምሮ ያካተተ በመሆኑ ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያግዝና በቀላሉ ተደራሽ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ ሰልጣኞችም የተሰጣቸውን ስልጠና ወደ ተግባር ከመቀየር ባሻገር ለማህበረሰቡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንዲሰሩ አስተባባሪው ጨምረው አሳስበዋል፡፡
በአደጋ ጊዜ የሚከሰት ሞትን በመጀመሪያ እርዳታ ህክምና ከ 40 እስከ 60% መቀነስ እንደሚቻል ነገር ግን ይህ ግንዛቤ በሀገራችን አደጋ በሚከሰትበት ቦታ በፍጥነት የሚገኙትን የመከላከያ ሰራዊት እና የፖሊስ አካላት ጨምሮ ዝቅተኛ እንደሆነ በአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም መምህር እና የስልጠናው ተሳታፊ አቶ አለበል አይናለም ገልፀዋል፡፡ አቶ አለበል አክለውም የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት ትምህርቱን ብቻ መማር በቂ እንዳልሆነ እና ከውስጥ የሚመነጭ ፍላጐት እንዲሁም በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ጠቁመው የትምህርት ክፍሉ ወደፊት ከዩኒቨርሲቲው እና ከአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም ከቀይ መስቀል ጋር በመሆን ግንዛቤ ለመፍጠር መሰራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡